በክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ከገቢዎች ባለስልጣ ቢሮ፣ የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና የፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር በገቢ አሰባሰብ ላይ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር የተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ የተቋማቱ አመራሮች ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ በገቢ አሰባሰብ ረገድ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በተደራጀ አኳኋን በመቅረፍ በቅንጅት ለመስራት እንደሚያስችል በፊርማ ስነስርአቱ መገለፁን ከክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መንግስት ለሀገር ልማትና እድገት እንዲሁም ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ለሚያካሂዳቸው የልማት ስራዎች እና አገልግሎት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የክልሉ ኢኮኖሚ ከተለያዩ መስኮች የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብበሰብ ጠንካራ ቅንጅታዊ ስራ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
ለዚህም በታክስ አሰባሰብ ስርዓት እና በሌሎች ከመንግስታዊ አገልግሎት የሚሰበሰቡ ገቢዎች ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የገቢ መጠን እያደገ መሄድ እንዳለበት በፊርማ ስነስርአቱ ተመላክቷል።
የገቢ አቅምን በማሳደግና የክልሉን የልማት ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረግ ጥረት በ2016 በጀት አመት በልዩ ሁኔታ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በሚካሄድ ስራ የክልሉን የገቢ እቅድ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረስ እንደታቀደ ተገልጿል።
ገቢን የሚሰበሰቡ ተቋማት የገቢ አቅማቸውን በአግባቡ ለይተው ጠንካራ ዕቅድ ላይ ተመርኩዘው ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው ተጠቅሶ ባለድርሻ አካላቱም የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በየጊዜው የዘርፉን አፈፃፀም መገምገም እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።