ዛሬ ጷጉሜ 5/2016 በገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ አስተባባሪነት በሀረር ከተማ ለብዙ ዘመናት የከተማዋ ችግር የሆነውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ መልክ በማስያዝ የህዝቡን ጤና በአግባቡ በመጠበቅ የደረቅ ቆሻሻ ፅዳት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በከተማዋ ከሚገኙ 6 ወረዳዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ የህያ በፈርማው ወቅት እንደገለጹት የዚህ ስራ ዋና ዓላማ በከተማዋ ለብዙ ከደረቅ ቆሻሻ አገልግሎት ጋር ምንም ዓይነት ገቢ ባለመሰብሰቡ ከተማዋ ለከፍተኛ ጉዳት ስትዳረግ ቆይታለች ከዚህ በኋላ ወረዳዎች ከየአካባቢያቸው የሚሰበስቡት ገቢ ለወረዳውና ለአካባቢው ፅዳትና ውበት እንዲሁም መሠረተ ልማት ማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የገለፁ ሲሆን ስራው በከፍተኛ ተነሳሽነት መስራት እንደሚገባው ገልፀዋል::
የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሊያስ ዮኒስ ሲገልጹ በቅርቡ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የወጣ የሀረር ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ደንብን ተከትሎ ከወረዳዎች ጋር ተግባብተን ወደዚህ ስራ መግባታችን ማዘጋጃ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ያቀደውን ከፍተኛ የገቢ ዕቅድ ለማሳካትና በከተማዋ የተጀመሩ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ የገለፁ ሲሆን በቀጣይ ከወረዳዎች ጋር በሌሎች የማዘጋጃ ቤት የገቢ ርዕሶች ላይም በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።