የሀረሪ ክልል ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር የማህበራዊ ተጠያቂነት በተመለከተ ትኩረት ከሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ኻሊድ አብዲ የማህበራዊ ተጠያቂነት በዜጎችና የህዝብ አገልጋዮች መካከል ገንቢ የሆኑ የሀሳብ ልውውጥ በማዳበር በድህነት ተኮር የአገልግሎት ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲገመግሙና እንዲያሻሽሉ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የፕሮግራም ዓላማ ሕብረተሰቡ ከመሰረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎትና መብቱን በማወቅ የአገልግሎት አሰጣጡን በመፈተሽ ችግሮችን በመለየት የተሻለ አገልግሎት አንዲያገኝ መጠየቅ እንዲችል በማድረግ መብቱን የሚያውቅ ጠያቂ ዜጋ በመፍጠር ማህበረሰቡ የዜጎችን ፍላጎት ያማከለ ፍትሀዊና ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሰፍን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ገልጸዋል
ፕሮግራሙ ማንኛውም አካል አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በአካባቢው ስለሚከናወኑ የልማት ስራዎች እና አገልግሎቶች መሻሻል ተገቢውን ጥያቄ እንዲነሳ ህብረተሰቡ ላይ ይሰራል ሲሉም ተስፋ ለህፃናት ድርጅት ተወካይ ወ/ሮ ዓይናለም ገመቹ ተናግረዋል።
የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ተሳትፎ ዜጎች የልማቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከዕቅድ ዝግጅት እስከ ትግበራው በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ በተፈለገው ደረጃ ለማሳደግ የሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል ።
በመድረኩ የክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮችና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣የሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች፣ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል ።