በሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጲያ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬዉ ዕለት መሰረታዊ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ኮንፈረንስ ተካሄዷል ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ፣ በክልል እንዲሁም በተቋም ደረጃ ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በጤና አገልግሎት ፣ በትምህርት፣ በመንገድ ፣በስራ እድል ፈጠራ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣በበጋ መስኖ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች ሪፖርት ቀርቧል።
በመድረኩ የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መሐመድ ያህያ የግማሽ የምርጫ ዘመን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር አፈፃፀም እና የቀሪ የምርጫ ዘመን ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙርያ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተሳታፊዎችን አወያይተዋል።
ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የማደግና የመበልፀግ ትልም እውን ለማድረግ ፣ የዲሞክራሲ ስርዓት መሰረት ለማስያዝ፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሣትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ በሚገኘው ሁለንተናዊ ስራዎች ላይ የአባላቱ ሚና ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡትን ተጨባጭ ለውጦች ፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና የቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
በየዘርፉ ተሞክሮ የሚሆኑ አበረታች ስራዎች እንዲሰፉና እንዲጠናከሩ በማድረግ ውስንነት ያለባቸው ስራዎችንም በቅንጅት የመስራት ላይ አባላቱ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው የቢሮው ሃላፊ አቶ መሐመድ ያህያ አመላክተዋል።
መንግስት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ተጠቃሚነት ላይ እያከናወነ የሚገኘው ስራ ተስፋ ሰጪና አበረታች መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባላቱ በየስራ ዘርፋቸው ተገቢውን አገልግሎት ለተገልጋዮች በመስጠት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ በሁሉም መሰረታዊ ድርጅት አባላት በሳል የሆነ ውይይት ተደርጎበት የጋራ መግባባት የተፈጠረ ሲሆን የኢንስፔክሽንና ስነ_ምግባር ኮሚሽን አመራሮች በመምረጥና ለጠቅላላው ኮንፈረንሱ መድረክ የሚሳተፉትን የመሰረታዊ ፓርቲ አባላትን በማስመረጥና አፅድቋል ።
በመጨረሻ የቢሮው የመሰረታዊ ድርጅት አባላት ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ኮንፈረንሱ ተጠናቋል።