የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የ2016 ስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 ኦቅዱን ለክልል ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርቱን ሰምቶ የቀጣይ አቅጣጫ አመላክቷል ።
ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መሐመድ ያህያ ባለ በጀት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚመደብላቸው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል እንዲችሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በበጀት አመቱ የደንበኞችን እርካታ ከማሳደግ አንፃር ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም ለክልሉ የተመደበውን በጀት ለታለመለት አላማና እቅድ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሰራ አውስተዋል፡፡
የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ከተቋማት ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲያውሉ እንደ ቢሮ የሚጠበቅባቸውን አሰራር በመዘርጋትና ክትትል በማድረግ እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል ።
ከክልል ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከተነሱ ጥያቄና ሀሳቦች መካከልም የፋይናንስ ግልጽነት አሰራር በተመለከተ ፣ የውስጥ ኦዲተሮች አቅም ከማጠናከር አንፃር፣ ፍትሐዊ የበጀት ድልድል በሚመለከት ፣ የመንግስት ንብረት አስተዳደርና በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ የአፈጻጸም ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው አባላቱ አስታውቋል።
ከክልል ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሱ ጥያቄና ሀሳቦች ላይ የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የማኔጅመንት አባላት ገለፃና ማብራሪያ አድርገዋል ።
በመጨረሻም ከቢሮው የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የክልል ምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈትሒያ ሳኒ በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል ክትትልናና ቁጥጥር ስራዎች በትኩረትና በአግባቡ ሊሰራና እንደሚገባና በጀት አመቱ የታዩ ክፍተቶች እንዲታረሙ የተገኙ ስኬቶች እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ፡