የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የዘንድሮውን የ100 ቀናት ስትራቴጂካዊ የድርጊት መርሃ-ግብር የመጀመሪያ 15 ቀናት አፈጻጸም ገመገመ። በግምገማው መድረክ ላይ የተቋሙ የዲጂታል አሰራር ሽግግር እና የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያዎች በዋና ትኩረትነት ተነስተዋል።
በግምገማ ላይ የቢሮ ኃላፊ አቶ ሀምዲ ሰላሀዲን እንዳሉት የ100 ቀናት ስትራቴጂካዊ የድርጊት መርሃ-ግብሩ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮና ኃላፊነት በላቀ የውጤታማነት ደረጃ እንዲወጣ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ዕቅዱ የመንግሥት ሥራዎችንና የልማት ፕሮጀክቶችን ሳያስተጓጉል ፈጣንና ተጨባጭ ለውጦችን ለማስመዝገብ በ30፣ 60፣ እና 100 ቀናት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል::
የቢሮ ኃላፊው አክለውም ቢሮው አሰራሩን በማዘመን የወረቀት አልባ እና የዲጂታል አሠራሮችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል ብለዋል። ማዕከላዊ የመረጃ ቋትን (Database) ከማዘመን ባለፈ የኤሌክትሮኒክስ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት (PMS)፣ እና የኤሌክትሮኒክስ ክፍያን (e-payment) በመተግበር የመንግሥት ፋይናንስና አስተዳደር ሥርዓት ግልጽና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም የደንበኞችንና የሠራተኞችን እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰው ጠቁመዋል::
ከዚህ ጎን ለጎን የውስጥ ኦዲት ቁጥጥርን ማጠናከር፣ ውዝፍ ዕዳዎችን ማጽዳት፣ እንዲሁም የክልሉን የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ለማሳደግ የማክሮ-ፊስካል ትንበያዎችን ማዘመን በእቅዱ ከተያዙ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው::
የፕሮግራም በጀት አተገባበርን በማጠናከር እንዲሁም የልማት አጋሮችንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን (CSOs) ተሳትፎ በማሳደግ የክልሉን የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ለማስፋትና የራስ አቅምን አስተማማኝ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል::
በመድረኩ ላይ የተቋሙ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር ወ/ሮ ሲትራ አብዱራህማን በዕቅዱ አፈጻጸም ዙሪያ ዝርዝር ሰነድ አቅርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል::
አንድ ጥራቱን የጠበቀ ዕቅድ ውጤታማነቱ የሚለካው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳና በጀት ወደ ተግባር ተቀይሮ ስራ ላይ ሲውል ነው” ያሉት የቢሮ ኃላፊው አቶ ሀምዲ የ100 ቀናት ዕቅዱ በተያዘለት ልክ ግቡን እንዲመታ በየሳምንቱ ጥብቅ ክትትልና ግምገማ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም የተጀመሩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል።







