መስከረም 23 ቀን 2019)፡- የሀረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግስት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የሰው ሐብት ትግበራ ፕሮግራም (Human Capital Operation) የ2019 በጀት ዓመት የቅድመ ዝግጅት ውይይት መድረክ በድሬዳዋ ከተማ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከክልሉ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮዎች፣ ከውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ ዳይሬክተሮች፣ የፕሮግራሙ ተጠሪዎች፣ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተሮች፣ የፋይናንስ ኦፊሰሮች እና የስራ ባልደረቦች ተሳትፈዋል።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዲረሂም የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ እና የተጣለውን ኃላፊነት በጥራት ለመወጣት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምክትልቢሮ ኃላፊው በንግግራቸው በርካታ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፡-
1. የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የ2018 በጀት ዓመት የኦዲት ዝግጅትን በሰዓቱና በጥራት ማጠናቀቅ፣
2. የዕቅድ ዝግጅትን ከእውነታው ጋር የተጣጣመ፣ ሊለካ የሚችል እና በተግባር ውጤት ላይ ያተኮረ ማድረግ፣
3.የግዥ እቅዶችን ከበጀት ጋር በማቀናጀት በጀትን ያለምንም ብክነትና መዘግየት ለታለመለት የልማት ዓላማ ማዋል፣
4. በሂደት ላይ ያሉ ስራዎችን አፈጻጸም በወቅቱ እየገመገሙ ሪፖርት ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ በጀት የተያዘለትና ባለብዙ ዘርፍ የሆነው የሰው ሐብት ትግበራ ፕሮግራም ስኬት በስራ ክፍሎች መካከል ባለው ጠንካራ ቅንጅት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ያህያ አጽንኦት ሰጥተዋል። በሰነድ የታቀደው እና ትግበራ ላይ የዋለው ስራ በመስክ ምልከታ በየጊዜው እየተረጋገጠ ፈጣን የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
በመድረኩ ላይ የፕሮግራሙ የውስጥ ኦዲተር ወ/ሮ ኢክራም ዚያድ፣ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ወ/ሮ አዲስዓለም ሰለሞን እና የቻናል አንድ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ በዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ ጽሁፍ አቅርበው ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የቻናል አንድ አስተባባሪው ለ2018 በጀት ዓመት ለሚደረገው ኦዲት ቅድመ ዝግጅት ልዩ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው በማስገንዘብ የመድረኩ ውይይት ተጠናቋል።








