በሀረሪ ክልል የመንግሥት ንብረት አስተዳደርን በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን የተደረገው ጥረት ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑ ተገለጸ
ሀረር፣ ነሀሴ 28/2018 (ገኢትቢሮ)፦ በሀረሪ ክልል ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት (DPMS) በግንባር ቀደምትነት ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ያህያ ገለጹ።
ቢሮው ከ“አፍሮኔክስ ቴክ ሀብ” ጋር በመተባበር በክልሉ በሚገኙ 16 ተቋማት ላይ አዲሱን የዲጂታል ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ለማዋል ዐበይት ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቋል። የዚህ ተነሳሽነት አካል የሆነና ከእነዚሁ 16 ተቋማት ለተውጣጡ 53 ባለሙያዎችና ኃላፊዎች—የግዥ፣ ፋይናንስ፣ ንብረት አስተዳደር ኃላፊዎች እና የአይቲ ባለሙያዎች—ሲሰጥ የቆየው በሁለት ዙር ተግባር ተኮር ሥልጠና በስኬት ተጠናቋል።
ተሳታፊዎች በስልጠናው ቆይታቸው የቋሚና አላቂ ንብረት ምዝገባ፣ ስልታዊ የንብረት ቆጠራ፣ የተሽከርካሪዎች መረጃ አያያዝ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ምዝገባ ዳታቤዝ አጠቃቀም ላይ ጥልቅ ግንዛቤ አግኝተዋል። ሥልጠናው ተቋማት የመንግስት ሀብት በጥራት፣ በብቃት እና በጥብቅ የቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲመሩ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል።
በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ያህያ፤ ይህ ሥልጠና ከዕለት ተዕለት የሥራ ልምምድ ወጣ ብሎ የሚከወን የተለመደ መድረክ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን ንብረት በዲጂታል ሥርዓት፣ በትክክለኛ መረጃ፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት ለመምራት የተጀመረ ቁልፍ የለውጥ ምዕራፍ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የመንግሥት ንብረት ኃላፊነት የአመራር ኃላፊነት ጭምር ነው ያሉት ሃላፊው በ16ቱ ተቋማት የትግበራ ሂደት ሲጀመር የተቋማት ኃላፊዎች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ቢሮውም በበኩሉ በየሳምንቱ ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የዲጂታል ሲስተም በራሱ ተአምር እንደማይሠራ የገለጹት አቶ መሀመድ ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃ በማስገባትና በኃላፊነት ስሜት ሲጠቀሙበት ብቻ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል አሳስበዋል። ከሥልጠናው አዳራሽ ሲወጡ እውነተኛው ሥራ እንደሚጀምር በማስታወስ ሰልጣኞች የቀሰሙትን እውቀት ወደ መሬት አውርደው በተግባር በመተርጎም ለሥርዓቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
በመድረኩ መገባደጃ ላይ በሥርዓቱ አጠቃቀም ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ከተሰጠ በኋላ የዕውቅና የሰርተፊኬት ማረጋገጫ ተበርክቷል። በክልሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ በመረጃ የሚመራ፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለማስረፅ የተጀመረው ይህ ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተረጋግጧል።

















