የሐረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርቱን በመገምገም የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት አካሄደ።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተቋሙ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱራሂም እንደገለፁት፣ የባለፈው በጀት ዓመት አፈፃፀም በአግባቡ መገምገም በሂደት የታዩ ክፍተቶችን ለማረም እንዲሁም የቢሮውን ጥንካሬዎች፣ ድክመቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች በመተንተን ለቀጣዩ ዓመት ስኬት ወሳኝ መሠረት ነው ብሎዋል።
ቢሮው በሚቀጥለው ዓመት ስራዎቹን በብቃት ለመፈጸም ባስቀመጠው ራዕይና ተልዕኮ መሠረት የተዘጋጀው የ2019 ዕቅድ፤ ለመንግስት ልማት የሚውለውን ፋይናንስ ማሳደግ እና አጠቃቀሙን ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ መዘጋጀቱ ተመላክቷል። በተጨማሪም የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ በሕግ የሚመራ እና ከብክነት የሚከላከል ሥርዓት እንዲዘረጋና እንዲጠናከር የሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት በዕቅዱ መካተታቸው ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተቋሙ ፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር ወ/ሮ ሲትራ አብዱራሀማን የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ በዝርዝር አቅርበዋል። የቀረበውን ሪፖርት እና እቅድ መነሻ በማድረግም ሰፊ አስተያየቶች፣ ማብራሪያዎች እና ጥያቄዎች ተነስተው ጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ሁሉም ዳይሬክቶሬቶች በውይይቱ የተሰጡትን አስተያየቶች እንደ ግብአት በመውሰድ እና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት በ2019 በጀት ዓመት የተሳካ ስራ ለመስራት ቃል በመግባት መድረኩ ተጠናቋል።









